መዝሙረ ዳዊት 97
1 እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ሐሤትን ታድርግ፥ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው።
2 ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።
3 እሳት በፊቱ ይሄዳል፥ ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል።
4 መብረቆቹ ለዓለም አበሩ፤ ምድር አየችና ተናወጠች።
5 ተራሮችም ከእግዚአብሔር ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።
6 ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ።
7 ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።
8 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው፤
9 አንተ፥ እግዚአብሔር፥ በምድር ላይ ሁሉ ልዑል ነህና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃልና።
10 እግዚአብሔርን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል።
11 ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።
12 ጻድቃን፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።