0:00

መዝሙረ ዳዊት 51

1 ለመዘምራን አለቃ፤ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።

2 ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤

3 እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።

4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።

5 እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።

6 እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ።

7 በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።

8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል።

9 ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

10 አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።

11 ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።

12 የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።

13 ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።

14 የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።

15 አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ያወራል።

16 መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።

17 የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።

18 አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።

19 የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።