0:00

መዝሙረ ዳዊት 6

1 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ ስምንተኛ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።

2 ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ።

3 ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው?

4 አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።

5 በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?

6 በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።

7 ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች፤ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ።

8 ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና።

9 እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ።

10 ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።