ትንቢተ ኤርምያስ 1
1 በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃል።
2 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን በመንግሥቱ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።
3 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ።
4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
5 በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።
6 እኔም። ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ።
7 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ። ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና። ብላቴና ነኝ አትበል።
8 እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር።
9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤
10 እነሆ። ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ።
11 ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል። ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ።
12 እግዚአብሔርም። እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ።
13 ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል። ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የሚፈላ አፍላል አያለሁ፥ ፊቱም ከሰሜን ወገን ነው አልሁ።
14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይገለጣል።
15 እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋ በቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ።
16 ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተው ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።
17 አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህም ሁሉ ንገራቸው፤ በፊታቸው እንዳላስፈራህ አትፍራቸው።
18 እነሆ፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ።
19 ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል እግዚአብሔር።