0:00

ትንቢተ ኤርምያስ 26

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ።

2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቁም፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ትነግራቸው ዘንድ ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ተናገራቸው፤ አንዲትም ቃል አትgWdል።

3 ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።

4 እንዲህም በላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፥

5 ያልሰማችሁትን በማለዳ ተነሥቼ ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባሪያዎቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፥

6 ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፥ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።

7 ካህናቱም ነቢያቱም ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ።

8 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ ካህናትና ነቢያት ሕዝቡም ሁሉ። ሞትን ትሞታለህ።

9 በእግዚአብሔር ስም። ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፥ ይህችም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ ስለ ምን ትንቢት ተናገርህ? ብለው ያዙት። ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰብስበው ነበር።

10 የይሁዳም አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፥ በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ።

11 ካህናቱና ነቢያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ። በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው ብለው ተናገሩ።

12 ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ። በሰማችሁት ቃል ሁሉ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል።

13 አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል።

14 እኔ ግን፥ እነሆ፥ በእጃችሁ ነኝ፤ በዓይናችሁ መልካምና ቅን የመሰለውን አድርጉብኝ።

15 ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በእርግጥ እወቁ።

16 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት። ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሞት አይገባውም አሉ።

17 ከአገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ።

18 ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ነቢይ ነበረ፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ።

19 በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተውምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።

20 ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፤ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገረ።

21 ንጉሡም ኢዮአቄም ኃያላኑም ሁሉ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ።

22 ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፤

23 ከግብጽም ኦርዮን አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው ሬሳውንም ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር ጣለው።

24 ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።