0:00

ትንቢተ ኤርምያስ 22

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥

2 እንዲህም በል። በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ አንተና ባሪያዎችህ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።

4 ይህንንም ነገር ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባሪያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ።

5 ነገር ግን ይህን ቃል ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ወና እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

6 እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና። አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ።

7 መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል።

8 ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን። እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደርገ? ይላሉ።

9 እነርሱም። የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላመለኩአቸውም ነዋ ብለው ይመልሳሉ።

10 ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና፥ የተወለደባትንም አገር አያይምና ለሚወጣ እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተ አታልቅሱ አትዘኑለትም።

11 በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና።

12 እንግዲህም ወደዚህ አይመለስም፥ በተማረከባት አገር ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።

13 ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤

14 ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ ለሚል፥ መስኮትንም ለሚያወጣ፥ በዝግባም ሥራ ለሚያሳጌጥ፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት!

15 በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ አይበላምና አይጠጣም ነበርን? ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር።

16 የድሀውንና የችግረኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።

17 ዓይንህና ልብህ ግን ለስስት ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።

18 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል። ወንድሜ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም። ጌታ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም።

19 አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።

20 ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን አንሺ፤ በዓባሪምም ውስጥ ሆነሽ ጩኺ።

21 በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም። አልሰማም አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ቃሌን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው።

22 በግ ጠባቂዎችሽን ሁሉ ነፋስ ይጠብቃቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ክፋትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትጐሳቈይማለሽ።

23 አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ፥ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕማም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታጓሪያለሽ!

24 እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ ማኅተም ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ እነቅልህ ነበር፥ ይላል እግዚአብሔር፤

25 ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ።

26 አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ።

27 ይመለሱባትም ዘንድ ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።

28 በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ለአንዳች የማይረባ የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለ ምን ተጥለው ወደቁ?

29 ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።

30 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወን በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመት በይሁዳም የሚነግሥ እንግዲህ አይገኝምና። መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።