0:00

ትንቢተ ኤርምያስ 52

1 ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የሊብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

2 ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

3 ከፊቱም አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

4 ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ዕርድ አደረገ።

5 ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር።

6 በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበር፥ ለአገሩም ሰዎች እንጀራ ታጣ።

7 ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ ሸሹ፥ በሁለቱም ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማይቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ።

8 የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉት፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ያዙ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ተበትነው ነበር።

9 ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለባት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ።

10 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በፊቱ ገደላቸው፥ የይሁዳንም አለቆች ሁሉ ደግሞ በሪብላ ገደላቸው።

11 የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሰንሰለት አሰረው ወደ ባቢሎንም ወሰደው፥ እስኪሞትም ድረስ በግዞት ቤት አኖረው።

12 በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረናው ከን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የቆመው የዘበኞቹ አለካ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

13 የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆችን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ።

14 ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ሁሉ ዙሪያዋን አፈረሱ።

15 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን የሕዝቡን ድኆች፥ በከተማም ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የሕዝቡንም ቅሬታ አፈለሰ።

16 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከአገሩ ድኆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።

17 ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የናስ ዓምዶች በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናሱን ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ።

18 ምንቸቶቹንና መጫሪያዎችንም መኰስተሪያዎችንና ድስቶችን ጭልፋዎችንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ።

19 የዘበኞቹም አለቃ ጽዋዎቹንና ማንደጃዎቹን ድስቶቹንና ምንቸቶችን መቅረዞችንና ጭልፋዎቹን መንቀሎችንም፥ የወርቁን ዕቃ በወርቅ፥ የብሩንም ዕቃ በብር አድርጎ፥ ወሰደ።

20 ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት ያሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኵሬ፥ ከመቀመጫዎቹም በታች የነበሩትን አሥራ ሁለቱን የናስ በሬዎች ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረም።

21 ዓምዶቹም፥ የአንዱ ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውፍረቱም አራት ጣት ያህል ነበረ፥ ባዶም ነበረ።

22 የናሱም ጕልላት በላዩ ነበረ፤ የአንዱም ጉልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው ሁሉ ከናስ የተሠሩ መረበብና ሮማኖች ነበሩበት፤ በሁለተኛውም ዓምድ ደግሞ እንደዚህ ያለ ነገርና ሮማኖች ነበሩበት።

23 በስተ ውጭም ዘጠና ስድስት ሮማኖች ነበሩ። በመረበቡም ዙሪያ የነበሩ ሮማኖች ሁሉ አንድ መቶ ነበሩ።

24 የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ፤

25 ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጀንደረባ፥ በከተማይቱም ከሚገኙት በንጉሡ ፊት ከሚቆሙት ሰባቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ።

26 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።

27 የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።

28 ናቡከደነፆር የማረከው ሕዝብ ይህ ነው፤ በሰባተኛው ዓመት ሦስት ሺህ ሀያ ሦስት አይሁድ፤

29 ናቡከደነፆርም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ነፍስ ከኢየሩሳሌም ማርኮአል፤

30 በናቡከደነፆር በሀያ ሦስተኛው ዓመት የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ከአይሁድ ሰባት መቶ አርባ አምስት ነፍስ ማርኮአል፤ ሰዎች ሁሉ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።

31 እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ አምስተኛው ቀን፥ የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴክ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳን ንጉሥ የዮአኪንን ራስ ከፍ ከፍ አደረገ ከወህኒም አወጣው፤

32 በመልካምም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት።

33 በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፥ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቴ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር።

34 የባቢሎንም ንጉሥ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እስኪሞት ድረስ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።