መጽሐፈ መሣፍንት 1

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።

2፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ።

3፤ ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ።

4፤ ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ።

5፤ አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው።

6፤ አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ።

7፤ አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ።

8፤ የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።

9፤ ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ።

10፤ ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ።

11፤ ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ።

12፤ ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ።

13፤ የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው።

14፤ እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት።

15፤ እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት።

16፤ የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ።

17፤ ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት።

18፤ ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ።

19፤ እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም።

20፤ ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ።

21፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል።

22፤ የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ።

23፤ የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር።

24፤ ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት።

25፤ የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው።

26፤ ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው።

27፤ ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።

28፤ እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም።

29፤ ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ።

30፤ ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ።

31፤ አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም።

32፤ በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ።

33፤ ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ።

34፤ አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው።

35፤ አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም።

36፤ የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።