0:00

ትንቢተ ኤርምያስ 10

1 እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ።

2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና።

3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እንጅ በመጥረቢያ ይሠራል።

4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል።

5 እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውማን ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።

6 አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው።

7 የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው?

8 በአንድ ጊዜ ሰንፈዋል፥ ደንቍረውማል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት የእንጨት ነገር ብቻ ነው።

9 የሠራተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው።

10 እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም።

11 እናንተም። ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ።

12 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

13 ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።

14 ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና።

15 እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ።

16 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

17 በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ፥ ዕቃሽን ከመሬት ሰብስቢ፤

18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በምድሪቱ የሚኖሩትን እስኪሰማቸው ድረስ በዚህ ጊዜ እወነጭፋቸዋለሁ፥ አስጨንቃቸውማለሁ።

19 ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቍስሌም ክፉ ነው፥ እኔ ግን። በእውነት የመከራ ቍስሌ ነው እርሱንም መሸከም ይገባኛል አልሁ።

20 ድንኳኔ ተበዘበዘ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፤ ልጆቼም ከእኔ ወጥተው አይገኙም፤ ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም።

21 እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል።

22 የወሬን ድምፅ ስሙ፤ እነሆም፥ የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ያደርጋቸው ዘንድ ከሰሜን ምድር ጽኑ ሽብር መጥቶአል።

23 አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።

24 አቤቱ፥ ቅጣኝ፤ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቍጣ አይሁን።

25 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ውጠውትማልና፥ አጥፍተውትማልና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አፍስስ።