0:00

ትንቢተ ኤርምያስ 34

1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና ከተሞችዋን ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።

2 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሂድ ለይሁዳም ንጉሥ ለሴዴቅያስ ተናገር እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ በእሳትም ያቃጥላታል፤

3 አንተም በእርግጥ ትያዛለህ በእጅም አልፈህ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም፤ ዓይንህም የባቢሎንን ንጉሥ ዓይን ታያለች፥ እርሱም ከአንተ ጋር አፍ ለአፍ ይናገራል፥ ወደ ባቢሎንም ትገባለህ።

4 ነገር ግን፥ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል። በሰይፍ አትሞትም፥ በሰላም ትሞታለህ እንጂ፤

5 ከአንተ በፊት እንደ ነበሩ እንደ ዱሮ ነገሥታት እንደ አባቶችህ መቃጠል፥ እንዲሁ ያቃጥሉሃልና። ወየው! ጌታ ሆይ እያሉ ያለቅሱልሃል፤ እኔ ቃልን ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።

6-

7 የባቢሎንም ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ፥ ከተመሸጉት ከይሁዳ ከተሞች የተረፉትን ለኪሶንና ዓዜቃን በወጋ ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ቃል ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው።

8-

9 ሰው ሁሉ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነች ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ፥ አይሁዳዊ ወንድሙንም ማንም እንዳይገዛ፥ ስለ አርነታቸው አዋጅ እንዲነገር ንጉሡ ሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።

10 ሰው ሁሉ ወንድ ባሪያውንና ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ ከእንግዲህ ወዲህም ማንም እንዳይገዛቸው ወደ ቃል ኪዳኑ የገቡ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሰሙ አርነትም አወጡአቸው።

11 ነገር ግን ከዚያ በኋላ ተመልሰው አርነት ያወጡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻቸውን አስመለሱ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም አድርገው ገዙአቸው።

12 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።

13 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁን ከባርነት ቤት ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ።

14 ሰባት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ የተሸጠላችሁን ስድስትም ዓመት የተገዛላችሁን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ አርነት ታወጡታላችሁ፥ እያንዳንዱም ያወጣዋል፤ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።

15 እናንተም ዛሬ ተመልሳችሁ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን አርነት ለማውጣት አዋጅ በመንገር ለዓይኔ ደስ የሚያሰኝን ነገር አድርጋችሁ ነበር፥ በስሜም በሚጠራበት ቤት ውስጥ በፊቴ ቃል ኪዳን አድርጋችሁ ነበር።

16 ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አስነቀፋችሁ፥ እያንዳንዳችሁም በፈቃዳቸው እንዲሄዱ አርነት ያወጣችኋቸውን ወንድና ሴት ባሪያዎቻችሁን አስመለሳችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም እንዲሆኑላችሁ ገዛችኋቸው።

17 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፤ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ መካከል እንድትበተኑ አደርጋችኋለሁ።

18 ቃል ኪዳኔንም የተላለፉትን ሰዎች፥ እንቦሳውንም ቈርጠው በቍራጩ መካከል ባለፉ ጊዜ በፊቴ ያደረጉትን የቃል ኪዳንን ቃል ያልፈጸሙትን፥

19 የይሁዳን አለቆችና የኢየሩሳሌምን አለቆች ጃንደረቦችን ካህናትንም በእንቦሳም ቍራጭ መካከል ያለፉትን የአገሩን ሕዝብ ሁሉ፥

20 ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።

21 የይሁዳንም ንጉሥ ሴዴቅያስንና አለቆቹን ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ ከእናንተም ለተመለሱት ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ።

22 እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደዚህችም ከተማ እመልሳቸዋለሁ፤ እርስዋንም ይወጋሉ ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የሌለበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።