0:00

መዝሙረ ዳዊት 127

1 የመዓርግ መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል።

2 በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ።

3 እነሆ፥ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፥ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።

4 በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው።

5 ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ብፁዕ ሰው ነው፤ ጠላቶቻቸውን በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ እርሱ አያፍርም።