0:00

መዝሙረ ዳዊት 141

1 የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ስማኝ፤ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ቃል አድምጥ።

2 ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።

3 አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።

4 ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፃን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር።

5 ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።

6 ኃያላኖቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፤ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ።

7 በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ።

8 አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፤ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት።

9 ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ።

10 እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ኃጢአተኞች በወጥመዳቸው ይውደቁ።