0:00

መዝሙረ ዳዊት 71

1 አስቀድመው ስለ ማረኩ ስለ አሚናዳብ ልጆች የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር።

2 በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም።

3 በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ፤ ኃይሌ መጠጊያዬ አንተ ነህና።

4 አምላኬ፥ ከኃጢአተኛ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ።

5 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና።

6 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው።

7 ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፤ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ።

8 አፌን ምስጋና ምላ ሁልጊዜ ክብርህንና ግርማህን እዘምር ዘንድ።

9 በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።

10 ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፤ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ።

11 እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።

12 አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

13 ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጕዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ።

14 እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ።

15 ሥራን አላውቅምና አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል።

16 በእግዚአብሔር ኃይል እገባለሁ፤ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ።

17 አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ።

18 እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ።

19 አቤቱ፥ እስከ አርያም ታላላቅ ነገሮችን አደረግህ፤ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?

20 ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።

21 ጽድቅህንም አብዛው፥ ተመልሰህም ደስ አሰኘኝ፥ ከጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።

22 እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ።

23 ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ።

24 ጕዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።