0:00

መዝሙረ ዳዊት 21

1 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል።

2 የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።

3 በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፤ ከክቡር ዕንቍ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።

4 ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም፥ ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።

5 በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት።

6 የዘላለም በረከትን ሰጥተኸዋልና። በፊትህም ደስታ ደስ ታሰኘዋለህ።

7 ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም።

8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው።

9 በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች።

10 ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ።

11 ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ።

12 ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ።

13 አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።