መዝሙረ ዳዊት 83
1 የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል።
2 እነሆ፥ ጠላቶችህ ጮኽዋልና፥ የሚጠሉህም ራሳቸውን አንሥተዋልና።
3 ሕዝብህን በምክር ሸነገሉአቸው፥ በቅዱሳንህም ላይ ተማከሩ።
4 ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፥ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ።
5 አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ፤ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፤
6 የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም፥ ሞዓብም አጋራውያንም፥
7 ጌባል አሞንም አማሌቅም፥ ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋር፤
8 አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ፥ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ሆኑአቸው።
9 እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፥ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው።
10 በዓይንዶር ጠፉ፥ እንደ ምድርም ጕድፍ ሆኑ።
11 አለቆቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ፥ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸው።
12 የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንወርሳለን የሚሉትን።
13 አምላኬ ሆይ፥ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው።
14 እሳት ዱርን እንደሚያቃጥል፥ ነበልባልም ተራሮች እንደሚያነድድ፥
15 እንዲሁ በቍጣህ አሳድዳቸው፥ በመቅሠፍትህም አስደንግጣቸው።
16 ፊታቸውን እፍረት ሙላው፥ አቤቱ፥ ስምህንም ይፈልጋሉ።
17 ይፈሩ ለዘላለሙም ይታወኩ፤ ይጐስቍሉ ይጥፉም።
18 ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፥ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።