0:00

መዝሙረ ዳዊት 36

1 ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። 1 ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም።

2 በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል።

3 የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው፤ ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ።

4 በመኝታው ጠማማነትን አሰበ፤ መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፤ ክፋትን አይንቃትም።

5 አቤቱ፥ ምሕረትህ በሰማይ ነው፥ እውነትህም ወደ ደመናት ትደርሳለች።

6 ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች፥ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት፤ አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ።

7 አቤቱ፥ ምሕረትህን እንዴት አበዛህ! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ።

8 ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ፥ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ።

9 የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።

10 ምሕረትህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ።

11 የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የኃጢአተኞችም እጅ አያውከኝ።

12 ዓመፃን የሚያደርጉ ሁሉ ከዚያ ወደቁ፤ ወድቀዋል፥ መቆምም አይችሉም።