መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 7
1፤ ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ።
2፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም።
3፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ። እርሱ መልካም ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና ብለውም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
4፤ ንጉሡም ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።
5፤ ንጉሡም ሰሎሞን ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ።
6፤ ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር።
7፤ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩን ውስጥ ቀደሰ፤ ሰሎሞንም የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ስቡንም መያዝ አልቻለምና የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ስብ በዚያ አቀረበ።
8፤ ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆኑ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያሉ እስራኤል ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።
9፤ ሰባት ቀንም መሠዊያውን ቀድሰው፥ ሰባት ቀንም በዓል አድርገው ነበርና በስምንተኛው ቀን የተቀደሰውን ጉባኤ አደረጉ።
10፤ በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛውም ቀን ሕዝቡን ወደ ድንኳናቸው አሰናበተ፤ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ደስ ብሎአቸው ሐሴትን እያደረጉ ሄዱ።
11፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ።
12፤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ።
13፤ ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥
14፤ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈግሉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።
15፤ አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ።
16፤ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
17፤ አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንደ ሄደ በፊቴ ብትሄድ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ብትጠብቅ፥
18፤ ከአባትህ ከዳዊት ጋር። በእስራኤል ላይ አለቃ፥ የሚሆን ከዘርህ አይታጣም ብዬ ቃል ኪዳን እንዳደረግሁ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።
19፤ እናንተ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትተዉ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥
20፤ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላችኋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፥ በአሕዛብም ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት አደርገዋለሁ።
21፤ ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውንም ይህን ቤት እያዩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ? ብለው ይደነቃሉ።
22፤ መልሰውም። ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።