መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 10
1፤ እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።
2፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ።
3፤ ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን።
4፤ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት።
5፤ እርሱም። ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6፤ ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
7፤ እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘላለም ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት።
8፤ እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።
9፤ እርሱም። አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው።
10፤ ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤
11፤ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።
12፤ ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
13፤ ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ።
14፤ አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው።
15፤ እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16፤ እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፥ ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ።
17 በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው።
18፤ ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ሰደደ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ።
19፤ እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።