0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 5

1፤ እንዲሁም ሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን የብርና የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰሎሞን አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አኖረው።

2፤ በዚያን ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች ሁሉ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

3፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተከማቹ።

4፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፥ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሡ።

5፤ ታቦቱንም የመገናኛውንም ድንኳን በድኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ።

6፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በታቦቱ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር።

7፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በቅድስት ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት።

8፤ ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፥ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር።

9፤ መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅዱስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ።

10፤ በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም።

11፤ በዚያም የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፥ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር፤

12፤ መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፥

13፤ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ። እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው።

14፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።