መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 20
1፤ እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ።
2፤ ወሬኞችም መጥተው። ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው ብለው ለኢዮሣፍጥ ነገሩት።
3፤ ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ።
4፤ ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ተከማቸ፤ ከይሁዳ ከተሞችም ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ።
5፤ ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤
6፤ እንዲህም አለ። አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም።
7፤ አምላካችን ሆይ፥ በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘላለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን?
8፤ እነርሱም የተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት።
9፤ ክፉ ነገር፥ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮኻለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ።
10፤ አሁንም፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ያልፉባቸው ዘንድ ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ፈቀቅ ብለው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥
11፤ እነሆ፥ ለወሮታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ያወጡን ዘንድ መጥተዋል።
12፤ አምላካችን ሆይ፥ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።
13፤ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።
14፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካሪያስ ልጅ በየሕዚኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤
15፤ እንዲህም አለ። ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል። ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም።
16፤ ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ ዓቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ።
17፤ እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው።
18፤ ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ።
19፤ ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በእጅግ ታላቅ ድምፅ ያመሰገኑት ዘንድ ቆሙ።
20፤ ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና። ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ።
21፤ ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፥ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ።
22፤ ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ።
23፤ የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ።
24፤ የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም።
25፤ ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ይሸከሙ ዘንድ አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር።
26፤ በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም እግዚአብሔርን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ።
27፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ።
28፤ በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ።
29፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ።
30፤ የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጥ አለች፥ አምላኩም በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
31፤ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።
32፤ በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን አደረገ።
33፤ ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላዘጋጁም ነበር።
34፤ የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል።
35፤ ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ።
36፤ ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠሩ ዘንድ አንድ ሆኑ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ።
37፤ የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር። ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም።