መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 28
1፤ አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም።
2፤ ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፥ ደግሞም ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችን ሠራ።
3፤ ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዐጠነ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ።
4፤ በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5፤ ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም መቱት፥ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞች ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡ። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ አመታት መታው።
6፤ የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ነበርና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሀያ ሺህ ገደለ፤ ሁሉም ጽኑዓን ነበሩ።
7፤ ከኤፍሬምም ወገን የነበረው ኃያል ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕርግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
8፤ የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፥ እጅግም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ።
9፤ በዚያም ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ገደላችኋቸው።
10፤ አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌም ልጆች ባሪያዎች ሆነው ይገዙላችሁ ዘንድ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን?
11፤ አሁንም ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።
12፤ ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የሰሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከሰልፍ በተመለሱት ላይ ተቃወሙአቸው።
13፤ ደግሞም። በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኃጢያታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የመቅሰፍቱም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነውና አሉአቸው።
14፤ ሰልፈኞቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤ ሁሉ ፊት ተዉ።
15፤ በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፥ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፥ አጎናጸፉአቸውም፥ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፥ መገቡአቸውም፥ አጠጡአቸውም፥ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፥ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማርያም ተመለሱ።
16፤ በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤
17፤ የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና።
18፤ ደግሞም ፍልስጥኤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር።
19፤ የይሁዳም ንጉሥ አካዝ እግዚአብሔርን ክዷልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቆአልና እግዚአብሔር ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው።
20፤ የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም።
21፤ አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኵሌታውን ገፈፈ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን አንዳች አልተጠቀመበትም።
22፤ ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ እግዚአብሔርን መበደል አበዛ።
23፤ ለመቱትም ለደማስቆ አማልክት። የሶርያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን ይረዱ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ።
24፤ አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ።
25፤ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ፤ የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።
26፤ የቀረውም ነገርና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኛውና የኋለኛው፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
27፤ አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በከተማይቱም በኢየሩሳሌም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።