መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 35
1፤ ኢዮስያስም ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ።
2፤ ካህናቱንም በየሥርዓታቸውም አቆመ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው።
3፤ እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ። ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤
4፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ ጻፈው ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፈው በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤
5፤ እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ የሌዋውያንም ነገድ በየወገናቸው እንደ ተከፈሉ እናንተ ተከፈሉ፤ ፋሲካውንም እረዱ፥
6፤ እናንተም ተቀደሱ፥ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ያደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።
7፤ ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ።
8፤ መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካሪያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ።
9፤ የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ።
10፤ አገልግሎቱም ተዘጋጀ፥ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሥ ትእዛዝ ቆሙ።
11፤ ፋሲካውንም አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ።
12፤ በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ።
13፤ ፋሲካውንም እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ።
14፤ ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ።
15፤ የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር።
16፤ እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ።
17፤ የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አደረጉ።
18፤ ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም።
19፤ ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ።
20፤ ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ።
21፤ እርሱም። የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።
22፤ ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጸናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ።
23፤ ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴናዎቹን። አጥብቄ ቈስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ አላቸው።
24፤ ብላቴኖቹም ከሰረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ።
25፤ ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል።
26፤ የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥
27፤ የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።