0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 12

1፤ እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።

2፤ እግዚአብሔርን በድለዋልና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

3፤ ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ።

4፤ ለይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ።

5፤ ነበዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።

6፤ የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ። እግዚአብሔር ጻድቅ ነው ብለው ሰውነታቸውን አዋረዱ።

7፤ እግዚአብሔርም ሰውነታቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል። ሰውነታቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፤

8፤ ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቁ ዘንድ ይገዙለታል ሲል ወደ ሸማያ መጣ።

9፤ የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ።

10፤ ንጉሡም ሮብዓም በእነርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው።

11፤ ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።

12፤ ሰውነቱንም ባዋረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ነገር ተገኘ።

13፤ ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች።

14፤ እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ።

15፤ የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ።

16፤ ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።