መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 15
1፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ ሆነ፤
2፤ አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው። አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።
3፤ እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር።
4፤ በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት።
5፤ በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ።
6፤ እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር።
7፤ እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።
8፤ አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ።
9፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ።
10፤ አሳም በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
11፤ በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር ሠዉ።
12፤ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ፤
13፤ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ።
14፤ ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ።
15፤ በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍት ሰጣቸው።
16፤ ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስላደረገች ከእቴጌነትዋ አዋረዳት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው።
17፤ በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ።
18፤ አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባ።
19፤ አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ሰልፍ አልነበረም።