0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። 19

1፤ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ።

2፤ ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን። ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ሆኖብሃል።

3፤ ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው።

4፤ ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ደግሞም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው።

5፤ በምድር ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ።

6፤ ፈራጆቹንም። ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ።

7፤ አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ አላቸው።

8፤ ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በእግዚአብሔር ስም ፍርድን እንዲፈርዱ ክርክርንም እንዲቈርጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ።

9፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ እግዚአብሔርን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ።

10፤ በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ በደምና በደም መካከል በሕግና በትእዛዝ በሥርዓትና በፍርድም መካከል ያለ ማናቸውም ነገር ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቍጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።

11፤ እነሆም፥ ለእግዚአብሔር በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።