መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 8

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው።

2፤ የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር።

3፤ ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።

4፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና።

5፤ እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት።

6፤ የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

7፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ።

8፤ ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል።

9፤ አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው።

10፤ ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው።

11፤ እንዲህም አለ። በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤

12፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ።

13፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል።

14፤ ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።

15፤ ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።

16፤ ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል።

17፤ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ።

18፤ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም።

19፤ ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥

20፤ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት።

21፤ ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ።

22፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች። እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።