መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 20
1፤ ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።
2፤ ዮናታንም። ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው።
3፤ ዳዊትም። እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም። ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ።
4፤ ዮናታንም ዳዊትን። ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው።
5፤ ዳዊትም ዮናታንን አለው። እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ።
6፤ አባትህም ቢፈልገኝ። ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው።
7፤ እርሱም። መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች እወቅ።
8፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ?
9፤ ዮናታንም። ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈጠረች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለ።
10፤ ዳዊትም ዮናታንን። አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው።
11፤ ዮናታንም ዳዊትን። ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ።
12፤ ዮናታንም ዳዊትን አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፤ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፤
13፤ አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።
14፤ እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፤
15፤ ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው።
16፤ ዮናታንም። እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
17፤ ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
18፤ ዮናታንም አለው። ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ።
19፤ ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፤ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ።
20፤ እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ።
21፤ እነሆም። ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፤ ብላቴናውንም። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም።
22፤ ብላቴናውን ግን። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ።
23፤ አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው።
24፤ ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፤ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ።
25፤ ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፤ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ።
26፤ ሳኦልም። አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፤ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም።
27፤ ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፤ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን። የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው።
28፤ ዮናታንም ለሳኦል። ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፤
29፤ እርሱም። ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፤ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት።
30፤ የሳኦልም ቍጣ በዮናታን ላይ ነደደና። አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኀፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን?
31፤ የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፤ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው።
32፤ ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት።
33፤ ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፤ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ።
34፤ አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቈጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም።
35፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ።
36፤ ብላቴናውንም። ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው።
37፤ ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን። ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ።
38፤ ዮናታንም ደግሞ። ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፤ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ።
39፤ ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር።
40፤ ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ። ወደ ከተማ ውሰድ አለው።
41፤ ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፤ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀሰ።
42፤ ዮናታንም ዳዊትን። በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።