መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 14
1፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም።
2፤ ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ።
3፤ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም።
4፤ ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ።
5፤ አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ።
6፤ ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ጭፍራ እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው።
7፤ ጋሻ ጃግሬውም። ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፤ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው።
8፤ ዮናታንም አለ። እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፤
9፤ እነርሱም። ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም።
10፤ ነገር ግን። ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፤ ምልክታችንም ይህ ይሆናል።
11፤ ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም። እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ ይወጣሉ አሉ።
12፤ የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን። ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው።
13፤ ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፤ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው።
14፤ የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ።
15፤ በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፤ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ።
16፤ በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ።
17፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ። እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።
18፤ በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል። ኤፉድን አምጣ አለው።
19፤ ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን። እጅህን መልስ አለው።
20፤ ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፤ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ።
21፤ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት አስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ።
22፤ ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኰበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ።
23፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፤ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር።
24፤ የእስራኤልም ሰዎች በዚያ ቀን ተጨነቁ፤ ሳኦል። ጠላቶቼን እስክበቀል እስከ ማታ ድረስ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን አምሎአቸው ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ መብል አልቀመሱም።
25፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ዱር ገባ፤ ማርም በምድር ላይ ነበረ።
26፤ ሕዝቡም ወደ ዱር በገባ ጊዜ እነሆ፥ የሚፈስስ ማር ነበረ፤ ሕዝቡ መሐላውን ፈርቶ ነበርና ማንም እጁን ወደ አፉ አላደረገም።
27፤ ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ባማለ ጊዜ አልሰማም ነበር፤ እርሱም በእጁ ያለችውን በትር ጫፍዋን ወደ ወለላው ነከረ፥ እጁንም ወደ አፉ አደረገ፤ ዓይኑም በራ።
28፤ ከሕዝቡም አንድ ሰው መልሶ። አባትህ። ዛሬ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን መሐላ አምሎአቸዋል አለው፤ ሕዝቡም ደከሙ።
29፤ ዮናታንም። አባቴ ምድሪቱን አስቸገረ፤ ከዚህ ማር ጥቂት ብቀምስ ዓይኔ እንደ በራ እዩ።
30፤ ይልቅስ ሕዝቡ ካገኙት ከጠላቶቻቸው ምርኮ በልተው ቢሆኑ የፍልስጥኤማውያን መመታት ይበልጥ አልነበረምን? አለ።
31፤ በዚያም ቀን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ መቱአቸው፤ ሕዝቡም እጅግ ደከሙ።
32፤ ሕዝቡም ለምርኮ ሳሱ፤ በጎችን በሬዎችንም ጥጆችንም ወስደው በምድር ላይ አረዱ፤ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ።
33፤ ለሳኦልም። እነሆ፥ ሕዝቡ ከደሙ ጋር በመብላታቸው እግዚአብሔርን በደሉ ብለው ነገሩት። ሳኦልም። እጅግ ተላለፋችሁ፤ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አቅርቡልኝ አላቸው።
34፤ ሳኦልም። በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ። እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን ወደ እኔ ያቅርብ፥ በዚህም እረዱና ብሉ፤ ከደሙም ጋር በመብላታችሁ እግዚአብሔርን አትበድሉ በሉአቸው አለው። እያንዳንዱም ሰው ሁሉ በእጁ ያለውን በሬውን በዚያች ሌሊት አቀረበ፥ በዚያም አረደው።
35፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ይኸውም ለእግዚአብሔር የሠራው መጀመሪያ መሠዊያ ነው።
36፤ ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን በሌሊት ተከትለን እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድ ሰው እንኳ አናስቀርላቸው አለ። እነርሱም። ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አድርግ አሉት። ካህኑም። ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ አለ።
37፤ ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን ልከተልን? በእስራኤልስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀው። በዚያ ቀን ግን አልመለሰለትም።
38፤ ሳኦልም። እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደ ሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም፤
39፤ እስራኤልን የሚያድን ሕያው እግዚአብሔርን! ኃጢአቱ በልጄ በዮናታን ቢሆን ፈጽሞ ይሞታል አለ። ከሕዝቡም ሁሉ አንድ የመለሰለት ሰው አልነበረም።
40፤ እስራኤልንም ሁሉ። እናንተ በአንድ ወገን ሁኑ፥ እኔና ልጄ ዮናታንም በሌላ ወገን እንሆናለን አለ። ሕዝቡም ሳኦልን ደስ የሚያሰኝህን አድርግ አሉት።
41፤ ሳኦልም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን። እውነትን ግለጥ አለው። ሳኦልና ዮናታንም ተያዙ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ።
42፤ ሳኦልም። በእኔና በልጄ በዮናታን መካከል ዕጣ ጣሉ አለ። ዮናታንም ተያዘ።
43፤ ሳኦልም ዮናታንን። ያደረግኸውን ንገረኝ አለው፤ ዮናታንም። በእጄ ባለው በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር በእርግጥ ቀምሻለሁ፤ እነሆኝ፥ እሞታለሁ ብሎ ነገረው።
44፤ ሳኦልም። እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ እንዲህም ይጨምርብኝ፤ ዮናታን ሆይ፥ ፈጽመህ ትሞታለህ አለ።
45፤ ሕዝቡም ሳኦልን። በውኑ በእስራኤል ዘንድ ታላቅ መድኃኒት ያደረገ ዮናታን ይሞታልን? ይህ አይሁን፤ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎአልና ሕያው እግዚአብሔርን! ከራሱ ጠጕር አንዲት በምድር ላይ አትወድቅም አሉት። ሕዝቡም እንዳይሞት ዮናታንን አዳነው።
46፤ ሳኦልም ፍልስጥኤማውያንን ከመከተል ተመለሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ሄዱ።
47፤ ሳኦልም መንግሥቱን በእስራኤል ላይ አጸና፤ በዙሪያውም ካሉት ከጠላቶቹ ሁሉ ጋር፥ ከሞዓብም፥ ከአሞንም ልጆች፥ ከኤዶምያስም፥ ከሱባም ነገሥታት፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ይዋጋ ነበር፤ በየሄደበትም ሁሉ ድል ይነሣ ነበር።
48፤ እርሱም ጀግና ነበረ፥ አማሌቃውያንንም መታ፥ እስራኤልንም ከዘራፊዎቹ እጅ አዳነ።
49፤ የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ የሱዊ፥ ሜልኪሳ ነበሩ፤ የሁለቱም ሴቶች ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ የታላቂቱ ስም ሜሮብ፥ የታናሺቱም ስም ሜልኮል ነበረ።
50፤ የሳኦልም ሚስት ስም የአኪማአስ ልጅ አኪናሆም ነበረ፤ የሠራዊቱም አለቃ ስም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ አበኔር ነበረ።
51፤ የሳኦልም አባት ቂስ ነበረ፤ የአበኔርም አባት ኔር የአቢኤል ልጅ ነበረ።
52፤ በሳኦልም ዕድሜ ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጽኑ ውጊያ ነበረ፤ ሳኦልም ጽኑ ወይም ኃያል ሰው ባየ ጊዜ ወደ እርሱ ይሰበስብ ነበር።