መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 25
1፤ ሳሙኤልም ሞተ፤ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
2፤ በማዖንም የተቀመጠ አንድ ሰው ነበረ፥ ከብቱም በቀርሜሎስ ነበረ፤ እጅግም ታላቅ ሰው ነበረ፥ ለእርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር።
3፤ የሰውዮውም ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ፤ የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፤ ሰውዮው ግን ባለጌ ነበረ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፤ ከካሌብም ወገን ነበረ።
4፤ ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ። ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ።
5፤ ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ። ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፤
6፤ እንዲህም በሉት። በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን።
7፤ አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፤ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም።
8፤ ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፤ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፤ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ።
9፤ የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ።
10፤ ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች። ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው።
11፤ እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው።
12፤ የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት።
13፤ ዳዊትም ሰዎቹን። ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ።
14፤ ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት። እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፤ እርሱ ግን ሰደባቸው።
15፤ እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፤ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፤
16፤ ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር።
17፤ ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቈርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ።
18፤ አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች።
19፤ ለብላቴኖችዋም። አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም።
20፤ እርስዋም በአህያው ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፤ እርስዋም ተገናኘቻቸው።
21፤ ዳዊትም። ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ።
22፤ ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው፥ እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር።
23፤ አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች።
24፤ በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ።
25፤ በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፤ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፤ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም።
26፤ አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ።
27፤ አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ።
28፤ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፤ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም።
29፤ ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፤ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል።
30፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥
31፤ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተካስህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ።
32፤ ዳዊትም አቢግያን አላት። ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።
33፤ ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።
34፤ ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር።
35፤ ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ። በደኅና ወደቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት።
36፤ አቢግያም ወደ ናባል መጣች፤ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፤ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፤ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር።
37፤ በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፤ ልቡም በውስጡ ሞተ፥
38፤ እንደ ድንጋይም ሆነ፤ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ።
39፤ ዳዊትም ናባል እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ። ከናባል እጅ የስድቤን ፍርድ የፈረደልኝ፥ ባሪያውንም ከክፋት የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እግዚአብሔርም የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰ አለ። ዳዊትም ልኮ ያገባት ዘንድ አቢግያን ተነጋገራት።
40፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ ቀርሜሎስ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ። ዳዊት ያገባሽ ዘንድ ወደ አንቺ ልኮናል ብለው ነገሩአት።
41፤ ተነሥታም በግምባርዋ ወድቃ እጅ ነሣችና። እነሆ፥ እኔ ገረድህ የጌታዬን ሎሌዎች እግር አጥብ ዘንድ አገልጋይ ነኝ አለች።
42፤ አቢግያም ፈጥና ተነሣች፤ በአህያም ላይ ተቀመጠች፥ አምስቱም ገረዶችዋ ተከተሉአት፤ የዳዊትንም መልእክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው።
43፤ ዳዊትም ደግሞ ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ወሰደ፤ ሁለቱም ሚስቶች ሆኑለት።
44፤ ሳኦል ግን የዳዊትን ሚስት ልጁን ሜልኮልን አገሩ ጋሊም ለነበረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።