መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 10
1፤ ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው። በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ።
2፤ ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ዳርቻ በጼልጻህ አገር ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም። ልትሻቸው ሄደህ የነበርህላቸ አህዮች ተገኝተዋል፤ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ። የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል።
3፤ ከዚያም ደግሞ ወደ ፊት ትሄዳለህ፤ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ፤ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች፥ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል፤
4፤ ሰላምታም ይሰጡሃል፥ ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላለህ።
5፤ ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል።
6፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።
7፤ እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምታገኘውን ሁሉ አድርግ።
8፤ በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፤ እኔም፥ እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፤ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደርገውን እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን ትቆያለህ።
9፤ ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፤ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት።
10፤ ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ።
11፤ ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው። የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን? ተባባሉ።
12፤ ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው። አባታቸውስ ማን ነው? ብሎ መለሰ። ስለዚህም። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን? የሚል ምሳሌ ሆነ።
13፤ ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው መስገጃ መጣ።
14፤ አጎቱም ሳኦልንና ብላቴናውን፥ ወዴት ሄዳችሁ ኖሮአል? አላቸው። እርሱም። አህዮችን ልንሻ ሄደን ነበር፤ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን አለ።
15፤ የሳኦልም አጎት። ሳሙኤል የነገረህን፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው።
16፤ ሳኦልም አጎቱን። አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው፤ ነገር ግን ሳሙኤል የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።
17፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ጠራ።
18፤ የእስራኤልንም ልጆች። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁ፥ ከግብጻውያንም እጅ ከሚያስጨንቁአችሁም ነገሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ።
19፤ ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ አታንግሥልን አላችሁት። አሁንም በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ አላቸው።
20፤ ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፥ ዕጣውም በብንያም ነገድ ላይ ወደቀ።
21፤ የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፥ ዕጣውም በማጥሪ ወገን ላይ ወደቀ። የማጥሪንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፥ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም።
22፤ ከእግዚአብሔርም። ገና ወደዚህ የሚመጣ ሰው አለን? ብለው ደግሞ ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል ብሎ መለሰ።
23፤ እነርሱም ሮጠው ከዚያ አመጡት፤ እርሱም በሕዝቡ መካከል ቆመ፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻው ወደ ላይ ከፍ ያለ ቁመተ ረጅም ነበረ።
24፤ ሳሙኤልም ለሕዝቡ ሁሉ። ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደሌለ እግዚአብሔር የመረጠውን ታያላችሁን? አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ። ንጉሥ ሕያው ይሁን እያሉ እልልታ አደረጉ።
25፤ ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፥ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው።
26፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካ ኃያላንም ከእርሱ ጋር ሄዱ።
27፤ ምናምንቴዎች ሰዎች ግን። ይህ ሰው እንዴት ያድነናል? ብለው ናቁት፥ እጅ መንሻም አላመጡለትም።