መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 26
1፤ የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጎአል አሉት።
2፤ ሳኦልም ተነሥቶ ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ይሻ ዘንድ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ።
3፤ ሳኦልም በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ በመንገዱ አጠገብ ሰፈረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፥ ሳኦልም በስተ ኋላው ወደ ምድረ በዳ እንደ መጣ አየ።
4፤ ዳዊትም ሰላዮች ሰደደ፥ ሳኦልም ወደዚህ እንደ መጣ በእርግጥ አወቀ።
5፤ ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ መጣ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አበኔርም የተኙበትን ስፍራ አየ፤ ሳኦልም በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6፤ ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን። ወደ ሳኦል ወደ ሰፈሩ ከእኔ ጋር የሚወርድ ማን ነው? ብሎ ጠየቃቸው፤ አቢሳም። እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ አለ።
7፤ ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፤ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩ በራሱ አጠገብ በምድር ተተክሎ በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ አበኔርና ሕዝቡም በዙርያው ተኝተው ነበር።
8፤ አቢሳም ዳዊትን። ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው።
9፤ ዳዊትም አቢሳን። እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው።
10፤ ደግሞም ዳዊት። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፤
11፤ እኔ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ።
12፤ ዳዊትም በሳኦል ራስ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውኃውን መንቀል ወሰደ፤ ማንም ሳያይ ሳያውቅም ሄዱ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ወድቆባቸው ነበርና ሁሉ ተኝተው ነበር እንጂ የነቃ አልነበረም።
13፤ ዳዊትም ወደዚያ ተሻገረ፤ በተራራውም ራስ ላይ ርቆ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ስፍራ ነበረ።
14፤ ዳዊትም ለሕዝቡና ለኔር ልጅ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ አትመልስምን? ብሎ ጮኸ። አበኔርም መልሶ። ለንጉሡ የምትጮኸው አንተ ማን ነህ? አለ።
15፤ ዳዊትም አበኔርን። አንተ ጕልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለ ምን ነው?
16፤ ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል፤ አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃው መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት አለው።
17፤ ሳኦልም የዳዊት ድምፅ እንደ ሆነ አውቆ። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለው። ዳዊትም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ድምፄ ነው አለው።
18፤ ደግሞ አለ። ጌታዬ ባሪያውን ስለ ምን ያሳድዳል? ምን አደረግሁ? ምንስ ክፋት በእጄ ላይ ተገኘብኝ?
19፤ አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የእኔን የባሪያህን ቃል ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አስነሥቶህ እንደ ሆነ፥ ቁርባንን ይቀበል፤ የሰው ልጆች ግን ቢሆኑ። ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ላይ እንዳልቀመጥ ዛሬ ጥለውኛልና በእግዚአብሔር ፊት ርጉማን ይሁኑ።
20፤ አሁንም በተራራው ላይ ሰው ቆቅን እንደሚሻ የእስራኤል ንጉሥ ነፍሴን ለመሻት ወጥቶአልና ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ አይፍሰስ።
21፤ ሳኦልም። በድያለሁ፤ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በዓይንህ ፊት ከብራለችና ከዚህ በኋላ ክፉ አላደርግብህም እነሆ፥ ስንፍና አድርጌአለሁ፥ እጅግ ብዙም ስቻለሁ አለ።
22፤ ዳዊትም መልሶ አለ። የንጉሥ ጦር እነሆ፥ ከብላቴኖችም አንድ ይምጣና ይውሰዳት።
23፤ ዛሬም እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ አልወደድሁምና ለሁሉ እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ጽድቁና እንደ እምነቱ ፍዳውን ይክፈለው።
24፤ ነፍስህም ዛሬ በዓይኔ ፊት እንደ ከበረች እንዲሁ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ትክበር፥ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።
25፤ ሳኦል ዳዊትን። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ቡሩክ ሁን፤ ማድረግን ታደርጋለህ፥ መቻልንም ትችላለህ አለው። ዳዊትም መንገዱን ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።