መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 27
1፤ ዳዊትም በልቡ። አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ።
2፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ።
3፤ ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ።
4፤ ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኰበለለ ሰማ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም።
5፤ ዳዊትም አንኩስን። በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፤ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው።
6፤ በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች።
7፤ ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቍጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበረ።
8፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር።
9፤ ዳዊትም ምድሪቱን መታ፤ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፤ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ።
10፤ አንኩስም። ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፤ ዳዊትም። በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ።
11፤ ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም።
12፤ አንኩስም። በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፤ ስለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።