ኦሪት ዘዳግም 33
1፤ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።
2፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።
3፤ ሕዝቡንም ወደዳቸው፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ ቃሎችህን ይቀበላሉ።
4፤ ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።
5፤ የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥ ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።
6፤ ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤ ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።
7፤ የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አግባው፤ እጆቹ ይጠንክሩለት፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8፤ ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤
9፤ ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።
10፤ ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።
11፤ አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥ የሚጠሉትም አይነሡ።
12፤ ስለ ብንያምም እንዲህ አለ። በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥ በትከሻውም መካከል ያድራል።
13፤ ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ በሰማያት ገናንነት በጠል፥ በታችኛውም ቀላይ፥
14፤ በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥ በጨረቃውም መውጣት ገናንነት
15፤ በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥
16፤ በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።
17፤ ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል፤ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18፤ ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።
19፤ የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።
20፤ ስለ ጋድም እንዲህ አለ። ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።
21፤ በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22፤ ስለ ዳንም እንዲህ አለ። ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።
23፤ ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ። ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።
24፤ ስለ አሴርም እንዲህ አለ። አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።
25፤ ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።
26፤ ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።
27፤ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ። አጥፋው ይላል።
28፤ እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
29፤ እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።