ኦሪት ዘዳግም 17
1፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ።
2፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከአገርህ ደጆች በማንኛይቱም ውስጥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ቃል ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት የሠራ ቢገኝ፥
3፤ ሄዶም ሌሎች አማልክትን ያመለከ፥ እኔ ላላዘዝኋቸው ለፀሐይና ለጨረቃ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የሰገደ ቢገኝ፥
4፤ ቢያወሩልህም ብትሰማም፥ ያንን ፈጽመህ መርምር፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ በእስራኤልም መካከል እንዲህ ያለ ርኵሰት እንደ ተሠራ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥
5፤ ይህን ክፉ ነገር የሠሩትን ያን ወንድ ወይም ያችን ሴት ወደ በርህ ታመጣቸዋለህ፥ እስኪሞቱም ድረስ በድንጋይ ትወግራቸዋለህ።
6፤ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ሞት የሚገባው ይገደል፤ በአንድ ምስክር አፍ አይገደል።
7፤ እርሱን ለመግደል በመጀመሪያ የምስክሮች እጅ በኋላም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ትሁንበት፤ እንዲሁም ክፋቱን ከመካከልህ አስወግድ።
8፤ በደምና በደም፥ በፍርድና በፍርድ፥ በመቍሰልና በመቍሰል መካከል በአገርህ ደጅ ውስጥ ሰዎች ስለሚከራከሩበት ክርክር የሚሳንህ የፍርድ ነገር ቢነሣ፥ አንተ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትወጣለህ፤
9፤ ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ ተሾመው ፈራጅ መጥተህ ትጠይቃለህ፤ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል።
10፤ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ የነገሩህን የፍርድ ነገር ታደርጋለህ፤ እንዳስተማሩህም ታደርግ ዘንድ ጠብቅ።
11፤ እንዳስተማሩህም ሕግ፥ እንደ ነገሩህም ፍርድ አድርግ፤ ከነገሩህ ፍርድ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
12፤ ማናቸውም ሰው ቢኰራ፥ በዚያም አምላክህን እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚቆመውን ካህኑን ወይም ፈራጁን ለመስማት ባይወድድ፥ ያ ሰው ይሙት፥ ከእስራኤልም ዘንድ ክፋትን አስወግድ፤
13፤ ሕዝቡም ሁሉ ሰምቶ ይፈራል፥ ከዚያም ወዲያ አይኰራም።
14፤ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በተቀመጥህባትም ጊዜ። በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ ንጉሥ አነግሣለሁ ስትል፥
15፤ አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ፤ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ንጉሥ ታነግሣለህ፤ ወንድምህ ያልሆነውን ከሌላ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም።
16፤ ነገር ግን ለእርሱ ፈረሶችን አያበዛም፤ እግዚአብሔር። በዚያ መንገድ ደግማችሁ አትመለሱም ብሎአችኋልና ፈረሶችን ለማብዛት ሕዝቡን ወደ ግብፅ አይመልስም።
17፤ ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያበዛም፤ ወርቅና ብርም ለእርሱ እጅግ አያበዛም።
18፤ በመንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ።
19፤
20፤ አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፥ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኰራ ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል፥ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረጅም ዘመን ይነግሡ ዘንድ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፥ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።