ኦሪት ዘዳግም 11
1፤ እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፥ ሕጉንም ሥርዓቱንም ፍርዱንም ትእዛዙንም ሁልጊዜ ጠብቅ።
2፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱንም፥ የጸናችም እጁን፥ የተዘረጋውንም ክንዱን፥
3፤ በግብፅም መካከል በንጉሡ በፈርዖንና በአገሩ ሁሉ ላይ ያደረጋትን ተአምራቱንና ሥራውን፥
4፤ በተከተሉአችሁም ጊዜ በኤርትራ ባሕር ውኃ እንዳሰጠማቸው፥ እግዚአብሔርም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳጠፋቸው፥ በግብፅ ጭፍራ በፈረሶቻቸውም በሰረገሎቻቸውም ያደረገውን፥
5፤ ወደዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በምድረ በዳ ያደረገላችሁን፥
6፤ በእስራኤልም ሁሉ መካከል ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን ድንኳኖቻቸውንም ለእነርሱም የነበራቸውን ሁሉ በዋጠቻቸው በሮቤል ልጅ በኤልያብ ልጆች በዳታንና በአቤሮን ያደረገውን ላላወቁትና ላላዩት ልጆቻችሁ አልነግራቸውምና እናንተ ዛሬ እወቁ።
7፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያደረጋትን ታላቂቱን ሥራ ሁሉ ዓይኖቻችሁ አይተዋል።
8፤
9፤ እንግዲህ እንድትጠነክሩ፥ ትወርሱአትም ዘንድ ወደምትሻገሩባት ምድር እንድትገቡ እንድትወርሱአትም፥ እግዚአብሔርም ለእነርሱና ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ በማለላቸው ወተትና ማርም በምታፈስሰው ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ።
10፤ ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፥ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደዘራህባት፥ በእግርህም እንዳጠጣሃት፥ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም።
11፤ ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች።
12፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው።
13፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዜን ፈጽማችሁ ብትሰሙ፥
14፤ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም ትሰበስብ ዘንድ በየጊዜው የበልጉን ዝናብና የክረምቱን ዝናብ ለምድራችሁ አወርዳለሁ።
15፤ በሜዳ ለእንስሶችህ ሣርን እሰጣለሁ፥ ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ።
16፤ ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም፥
17፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፤ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ።
18፤ እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፥ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁኑ።
19፤ ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው።
20፤
21፤ እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፥ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፥ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።
22፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥
23፤ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፥ ከእናንተም የሚበልጡትን የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ።
24፤ የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል።
25፤ በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል።
26፤ እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤
27፤ በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ፤
28፤ መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬም ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቋቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው።
29፤ አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ አንተን ወደምትሄድባት ምድር ባገባህ ጊዜ፥ በረከቱን በገሪዛን ተራራ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ።
30፤ እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከፀሐይ መግቢያ ካለችው መንገድ በኋላ፥ በዓረባ በተቀመጡት በከነዓናውያን ምድር፥ በጌልገላ ፊት ለፊት በሞሬ የአድባር ዛፍ አጠገብ ናቸው።
31፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፥ ትወርሱአታላችሁም፥ ትቀመጡባታላችሁም።
32፤ እኔም ዛሬ በፊታችሁ የማኖራትን ሥርዓትና ፍርድ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።