ኦሪት ዘዳግም 32

1፤ ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።

2፤ ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥ ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።

3፤ የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ።

4፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።

5፤ እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው።

6፤ ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።

7፤ የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።

8፤ ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ።

9፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው።

10፤ በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።

11፤ ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው።

12፤ እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።

13፤ በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የእርሻውን ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥ ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤

14፤ የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ።

15፤ ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።

16፤ በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት።

17፤ እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ።

18፤ የወለደህን አምላክ ተውህ፥ ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።

19፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው።

20፤ እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤ ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤ ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸው።

21፤ አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤

3ቍ.

15፤ በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል። በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤ እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።

22፤ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥ የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።

23፤ መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤ በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ።

24፤ በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤ በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤ የአራዊትን ጥርስ፥ የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ።

25፤ ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል።

26፤ እበትናቸዋለሁ አልሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ።

27፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ። እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም እንዳይሉ፥ ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ።

28፤ ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም።

29፤ አእምሮ ቢኖራቸው፥ ይህንን ያስተውሉ ነበር፥ ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር።

30፤ እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥ እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር?

31፤ አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤ ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው።

32፤ ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ነው፤ ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤ ዘለላውም መራራ ነው።

33፤ የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥ የእፉኝትም ሥራይ ነው።

34፤ ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን? በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?

35፤ የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥ የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና እግራቸው ሲሰናከል በቀልና ፍርድ የእኔ ነው።

36፤ ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥ የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።

37፤ እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?

38፤ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ።

39፤ አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።

40፤ እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና

41፤ የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።

42፤ ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤ ከጠላት አለቆችም ራስ ሰይፌ ሥጋ ይበላል።

43፤ የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።

44፤ ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ።

45፤ ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ።

46፤ እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት።

47፤ ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ።

48፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

49፤ ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤

50፤ ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤

51፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥

52፤ ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።