ኦሪት ዘዳግም 27
1፤ ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ብለው ሕዝቡን አዘዙ። ዛሬ ያዘዝኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ።
2፤ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ ታላላቅ ድንጋዮችን ለአንተ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው።
3፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ትገባ ዘንድ በተሻገርህ ጊዜ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ጻፍባቸው።
4፤ ዮርዳኖስንም በተሻገርህ ጊዜ፥ ዛሬ እንዳዘዝሁህ፥ እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው።
5፤ በዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ መሠዊያውም ብረት ካልነካው ድንጋይ ይሁን።
6፤ ካልተጠረበም ድንጋይ የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ሥራ፤ ለአምላክም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት፤
7፤ የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዋበት፥ በዚያም ብላ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ።
8፤ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ የተገለጠ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ።
9፤ ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል።
10፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ።
11፤ ሙሴም በዚያን ቀን እንዲህ ብሎ ሕዝቡን አዘዘ።
12፤ ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ እነዚህ፥ ስምዖንና ሌዊ ይሁዳና ይሳኮር ዮሴፍና ብንያም፥ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ።
13፤ ይረግሙም ዘንድ እነዚህ፥ ሮቤልና ጋድ አሴርና ዛብሎን ዳንና ንፍታሌም፥ በጌባል ተራራ ላይ ይቁሙ።
14፤ ሌዋውያንም ከፍ ባለች ድምፅ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገራሉ።
15፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ።
16፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
17፤ የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
18፤ ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
19፤ በመጻተኛ በድሀ አደጉም በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
20፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ልብስ ገልጦአልና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
21፤ ከማናቸይቱም እንስሳ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
22፤ ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
23፤ ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
24፤ ባልንጀራውን በስውር የሚመታ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
25፤ የንጹሑን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
26፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።