ኦሪት ዘዳግም 28

1፤ እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።

2፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል።

3፤ አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ።

4፤ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል።

5፤ እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል።

6፤ አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ።

7፤ እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ።

8፤ እግዚአብሔር በረከቱ በአንተ ላይ በጐተራህ በእጅህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ያዝዛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል።

9፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።

10፤ የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል።

11፤ እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ እግዚአብሔር በጎነቱን በላይህ ያበዛል።

12፤ እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብ ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዝብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም።

13፤

14፤ ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም።

15፤ ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።

16፤ በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ።

17፤ እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል።

18፤ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል።

19፤ አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ።

20፤ እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል።

21፤ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል።

22፤ እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል።

23፤ በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፥ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች።

24፤ እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል፤ እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25፤ እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል፤ በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፥ በሰባት መንገድ ከእነርሱ ትሸሻለህ፤ ለምድርም መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ።

26፤ ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራቸውም የለም።

27፤ እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል።

28፤ እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል።

29፤ በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም።

30፤ ሚስት ታጫለህ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል፤ ቤት ትሠራለህ፥ አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፥ ከእርሱም አትበላም።

31፤ በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚያድንህም አታገኝም።

32፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፥ ዓይኖችህም ያያሉ፥ ሁልጊዜም ስለ እነርሱ ሲባክኑ ያልቃሉ፤ በእጅህም ኃይል ምንም አይገኝም።

33፤ የምድርህን ፍሬ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ የተገፋህም ትሆናለህ።

34፤ ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ።

35፤ እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል።

36፤ እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ።

37፤ እግዚአብሔርም በሚያገባህ በአሕዛብ መካከል ሁሉ ድንጋጤ ምሳሌም ተረትም ትሆናለህ።

38፤ እጅግ ዘር ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ።

39፤ ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ፤ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፥ የወይን ጠጁንም አትጠጣም።

40፤ የወይራ ዛፍ በአገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ወይራህም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም።

41፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይወለዱልሃል፤ በምርኮም ይሄዳሉና ለአንተ አይሆኑልህም።

42፤ ዛፍህን ሁሉ የምድርህንም ፍሬ ኩብኩባ ይወርሰዋል።

43፤ በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አንተም ዝቅ ዝቅ ትላለህ።

44፤ እርሱ ያበድርሃል፥ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፥ አንተም ጅራት ትሆናለህ።

45፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዓቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፥ ያሳድዱህማል፥ ያገኙሁማል።

46፤ በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ።

47፤ ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና

48፤ በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል።

49፤

50፤ እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን፥ ፊታቸው የደነደነውን፥ ሽማግሌውንም የማያፍሩትን፥ ሕፃኑንም የማይምሩትን ሕዝብ ንስር እንደሚበርር ከሩቅ አገር ከምድር ዳር ያመጣብሃል።

51፤ እስክትጠፋ ድረስ የከብትህን ፍሬ የምድርህንም ፍሬ ይበላሉ፤ እስኪያጠፉህም ድረስ እህልን የወይንም ጠጅ ዘይትንም የላምህንና የበግህን ርቢ አይተዉልህም።

52፤ በአገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ደጆች ሁሉ ከብበው ያስጭንቁሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ በደጆች ሁሉ ከብበው ያስጨንቁሃል።

53፤ ጠላቶችህም ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።

54፤ በአንተ ዘንድ የተለሳለሰና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ይኖር የነበረ ሰው በወንድሙ፥ አቅፋውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆች ይቀናል፤

55፤ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም።

56፤ በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ትኖር የነበረችው፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥

57፤ በወንድና በሴት ልጅዋም፥ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፥ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።

58፤ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም <<አምላክህ እግዚአብሔር>> የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥

59፤ እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል።

60፤ የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል።

61፤ ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል።

62፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል።

63፤ እግዚአብሔርም በጎ ያደርግላችሁ ዘንድ ያበዛችሁም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋችሁ ሲያፈርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።

64፤ እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወዳሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን፥ ታመልካለህ።

65፤ በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፥ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ፥ ፈዛዛ ዓይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል።

66፤ ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም፤

67፤ አንተ ስለ ፈራህበት ስለ ልብህ ፍርሃት፥ በዓይንህም ስለምታየው አስተያየት፥ ማለዳ። መቼ ይመሻል? ትላለህ፤ ማታም። መቼ ይነጋል? ትላለህ።

68፤ ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።