መጽሐፈ ምሳሌ 7
1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ።
2 ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፤ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፤
3 በጣቶችህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
4 ጥበብን። አንቺ እኅቴ ነሽ በላት፥ ማስተማውልንም። ወዳጄ ብለህ ጥራት፥
5 ከጋለሞታ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ቃልዋን ካለዘበች ከሌላይቱ ሴት።
6 በቤቴ መስኮት ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፤
7 ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፤ ከጐበዛዝትም መካከል ብላቴናውን አእምሮ ጐድሎት አየሁ፥
8 በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፥
9 ማታ ሲመሽ፥ ውድቅትም ሲሆን፥ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ።
10 እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች።
11 ሁከተኛና አባያ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤
12 አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች።
13 ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው።
14 መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ።
15 ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም።
16 በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ።
17 በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ።
18 ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን።
19 ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤
20 በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
21 በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች።
22 እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥
23 ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ።
24 ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ።
25 ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል በጎዳናዋ አትሳት።
26 ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው።
27 ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።