መጽሐፈ ምሳሌ 3
1 ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።
2 ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።
3 ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
4 በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።
5 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤
6 በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።
7 በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤
8 ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም ጠገን።
9 እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት፤
10 ጐተራህም እህልን ይሞላል፥ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች።
11 ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።
12 እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።
13 ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤
14 በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና።
15 ከቀይ ዕንቍም ትከብራለች፥ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
16 በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር።
17 መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።
18 እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው።
19 እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።
20 በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
21 ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ።
22 ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ።
23 የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም።
24 በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ፥ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆንልሃል።
25 ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኃጥኣን ጥፋት አትፈራም፤
26 እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።
27 ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፥ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን።
28 ወዳጅህን። ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ አትበለው። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ።
29 በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ፥ እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ።
30 ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ፥ እርሱ ክፉ ካልሠራብህ።
31 በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ።
32 ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው።
33 የእግዚአብሔር መርገም በኃጥእ ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል።
34 በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
35 ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ የሰነፎች ከፍታቸው ግን መዋረድ ነው።