መጽሐፈ ምሳሌ 2
1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥
2 ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።
3 ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥
4 እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤
5 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።
6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤
7 እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤
8 የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል።
9 የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።
10 ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤
11 ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥
12 ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤
13 እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተው፥
14 ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥
15 መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፤
16 ከጋለሞታ ሴት አንተን ለመታደግ፥ ቃልዋን ከምታለዝብ ከሌላዪቱም ሴት፤
17 የሕፃንነት ወዳጅዋን የምትተው የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳ፤
18 ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፥ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ።
19 ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ የሕይወትንም ጎዳና አያገኙም፤
20 አንተም በደጋግ ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ።
21 ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፥ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤
22 ኃጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።