መጽሐፈ ምሳሌ 10
1 የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው።
2 በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል።
3 እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኅጥኣንን ምኞት ግን ይገለብጣል።
4 የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች።
5 በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል።
6 በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኅጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
7 የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኅጥኣን ስም ግን ይጠፋል።
8 በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የሚሰንፍ ግን ይወድቃል።
9 ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል።
10 በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፤ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል።
11 የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ የኃጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
12 ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች።
13 በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።
14 ጠቢባን እውቀትን ይሸሽጋሉ፤ የሰነፍ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል።
15 የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው።
16 የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኃጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው።
17 ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል።
18 ጥልን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፤ ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው።
19 በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።
20 የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኅጥኣን ልብ ግን ምናምን ነው።
21 የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፤ ሰነፎች ግን ከልባቸው ጕድለት የተነሣ ይሞታሉ።
22 የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።
23 ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው።
24 የኀጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች።
25 ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኃጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘላለም መሠረት ነው።
26 ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥ እንዲሁም ታካች ለላኩት።
27 እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች።
28 የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል።
29 የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ።
30 ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኅጥኣን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም።
31 የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች።
32 የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥኣን አፍ ግን ጠማማ ነው።