መጽሐፈ ምሳሌ 15
1 የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች።
2 የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፤ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል።
3 የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ።
4 ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል።
5 ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው።
6 በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።
7 የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፤ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።
8 የኅጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።
9 የኅጥኣን መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል።
10 ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥ ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል።
11 ሲኦልና ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት የታወቁ ናቸው፤ ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው።
12 ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥ ወደ ጠቢባንም አይሄድም።
13 ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፤ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች።
14 የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል።
15 ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው።
16 እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል።
17 የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።
18 ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል።
19 የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፤ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት።
20 ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል።
21 ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል።
22 ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል።
23 ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፤ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!
24 በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል።
25 እግዚአብሔር የትዕቢተኞች ቤት ይነቅላል፤ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል።
26 የበደለኛ አሳብ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናት፤ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው።
27 ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፤ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።
28 የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል የኅጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል።
29 እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።
30 የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል።
31 የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል።
32 ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል።
33 እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፤ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።