መጽሐፈ ምሳሌ 18
1 መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።
2 ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፤ በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ።
3 ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር።
4 የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፥ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው።
5 የጻድቅ ፍርድ ይጠምም ዘንድ፥ ለኀጥእም ማድላት መልካም አይደለም።
6 የሰነፍ ከንፈር በጥል ውስጥ ትገባለች፥ አፉም በትርን ትጠራለች።
7 የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው።
8 የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል።
9 በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው።
10 የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።
11 ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፥ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር።
12 ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።
13 ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል።
14 የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፤ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል?
15 የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች።
16 የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች።
17 ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፤ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል።
18 ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥ በኃያላንም መካከል ትበይናለች።
19 የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፤ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው።
20 የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል።
21 ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ።
22 ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል።
23 ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፤ ባለጠጋ ግን በድፍረት ይመልሳል።
24 ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።