ኦሪት ዘጸአት 9
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2፤ ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥
3፤ እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል።
4፤ እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም።
5፤ እግዚአብሔርም። ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ።
6፤ እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም።
7፤ ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
8፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።
9፤ እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል አላቸው።
10፤ ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ።
11፤ ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና።
12፤ እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም።
13፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
14፤ በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ።
15፤ አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤
16፤ ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ።
17፤ እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን?
18፤ እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ።
19፤ በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል።
20፤ ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤
21፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ።
22፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ አለው።
23፤ ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ።
24፤ በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ።
25፤ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።
26፤ የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም።
27፤ ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ። በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን።
28፤ የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እለቅቃችሁማለሁ፥ ከዚያም በኋላ በዚህ አትቀመጡም አላቸው።
29፤ ሙሴም። ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር እንደሆነች ታውቅ ዘንድ ነጎድጓዱ ይቀራል፥ በረዶውም ደግሞ አይወርድም።
30፤ ነገር ግን አንተና ባሪያዎችህ አምላክን እግዚአብሔርን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁ አለው።
31፤ ገብሱ እሸቶ ተልባውም ኣፍርቶ ነበርና ተልባና ገብሱ ተመታ።
32፤ ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም።
33፤ ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ተቋረጠ፥ ዝናቡም በምድር ላይ አልፈሰሰም።
34፤ ፈርዖንም ዝናቡ በረዶውም ነጎድጓዱም እንደ ተቋረጠ ባየ ጊዜ ኃጢያትን ጨመረ፥ እርሱና ባሪያዎቹም ልባቸውን አደነደኑ።
35፤ የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደተናገር የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።