ኦሪት ዘጸአት 11
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሰፍት አመጣለሁ፥ ከዚያ ወዲያም ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አባርሮ ይሰድዳችኋል።
2፤ ወንዱ ከወዳጁ ሴቲቱም ከወዳጅዋ የብርና የወርቅ ዕቃ ይሹ ዘንድ በሕዝቡ ጆሮ ተናገር አለው።
3፤ እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠው። ሙሴም በፈርዖን ባሪያዎችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ አገር እጅግ የከበረ ሰው ነበረ።
4፤ ሙሴም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእኩል ሌሊት እኔ በግብፅ መካከል እወጣለሁ፤
5፤ በግብፅም አገር ያለ በኵር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባሪያይቱ በኵር ድረስ፥ የከብቱም በኵር ሁሉ ይሞታል።
6፤ በግብፅም አገር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ ኋላም ደግሞ የማይሆን ታላቅ ጩኸት ይሆናል።
7፤ እግዚአብሔር ግን በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል እንዲለይ እንድታውቁ በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም።
8፤ እነዚህም ባሪያዎችህ ሁሉ። አንተ ውጣ የሚከተሉህም ሕዝብ ሁሉ ይውጡ እያሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፥ ለእኔም ይሰግዳሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ። ሙሴም በጽኑ ቁጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
9፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ተአምራቴ በግብፅ አገር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም አለው።
10፤ ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ አልለቀቀም።