ኦሪት ዘጸአት 37
1፤ ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ።
2፤ በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት።
3፤ አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ።
4፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
5፤ ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ።
6፤ ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ።
7፤ ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው።
8፤ ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው።
9፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ።
10፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ።
11፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት።
12፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት።
13፤ አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ።
14፤ ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ።
15፤ ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።
16፤ ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን ጽዋዎቹንም መቅጃዎቹንም፥ ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው።
17፤ መቅረዙንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጕብጕቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ።
18፤ በስተ ጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ወጡ።
19፤ በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ።
20፤ በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ።
21፤ ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ።
22፤ ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር።
23፤ ሰባቱንም መብራቶች መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ።
24፤ መቅረዙንም ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ።
25፤ የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ።
26፤ ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት።
27፤ ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ነበሩ።
28፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
29፤ የተቀደሰውንም የቅብዓቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ።