ኦሪት ዘጸአት 21

1፤ በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው።

2፤ ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ።

3፤ ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ።

4፤ ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ፥ እርሱም ብቻውን ይውጣ።

5፤ ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥

6፤ ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን።

7፤ ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ።

8፤ ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም።

9፤ ለልጁም ብድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት።

10፤ ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት።

11፤ ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ።

12፤ ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።

13፤ ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ።

14፤ ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውን በተንኰል ቢገድለው፥ እንዲሞት ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው።

15፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።

16፤ ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።

17፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል።

18፤ ሁለት ሰዎችም ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን ታምሞ በአልጋው ላይ ቢተኛ፥

19፤ ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይከፍለው ዘንድ፥ ያስፈውሰውም ዘንድ ግዴታ አለበት።

20፤ ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ።

21፤ የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ።

22፤ ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል።

23፤ ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥

24፤ ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥

25፤ እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።

26፤ ሰውም የባሪያውን ወይም የባሪይይቱን ዓይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ አርነት ያውጣው።

27፤ የባሪያውን ወይም የባሪያይቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ አርነት ያውጣው።

28፤ በሬም ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው።

29፤ በሬው ግን አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባይጠብቀውም፥ ወንድንም ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል።

30፤ ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ዎጆ የጫኑበትን ያህል ይስጥ።

31፤ ደግሞ ወንድን ልጅ ቢወጋ ሴትንም ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት።

32፤ በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር።

33፤ ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅበት፥

34፤ የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን።

35፤ የሰው በሬ የሌላውን በሬ እስኪሞት ድረስ ቢወጋ፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ።

36፤ በሬውም አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው።