ኦሪት ዘጸአት 8
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው። ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2፤ ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤
3፤ ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤
4፤ ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።
5፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ በለው።
6፤ አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፥ የግብፅንም አገር ሸፈኑ።
7፤ ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ።
8፤ ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ አላቸው።
9፤ ሙሴም ፈርዖንን። ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ አለው። እርሱም። ነገ አለ።
10፤ ሙሴም። አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን።
11፤ ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ አለ።
12፤ ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
13፤ እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ።
14፤ እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች።
15፤ ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም።
16፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው።
17፤ እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ።
18፤ ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ።
19፤ ጠንቋዮችም ፈርዖንን። ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።
20፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
21፤ ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ በባሪያዎችህም በሕዝብህም በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ።
22፤ በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ።
23፤ በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል።
24፤ እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች።
25፤ ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ሂዱ፥ በአገሩ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ አላቸው።
26፤ ሙሴም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችን የግብፃውያንን ርኵሰት እንሰዋለንና እንዲህ ይደረግ ዘንድ አይገባም፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኵሰት በፊታቸው ብንሠዋ አይወግሩንምን?
27፤ እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እንደሚያዝዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን አለ።
28፤ ፈርዖንም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፥ ጸልዩልኝ አለ።
29፤ ሙሴም። እነሆ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፥ የዝንቡም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከሕዝቡም ነገ እንዲሄዱ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን አለ።
30፤ ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
31፤ እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ የዝንቡንም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከህዝቡም አስነሣ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም።
32፤ ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።