ኦሪት ዘጸአት 38

1፤ ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ።

2፤ ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው።

3፤ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ።

4፤ እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያ አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው።

5፤ ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ።

6፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በናስም ለበጣቸው።

7፤ ይሸከሙትም ዘንድ በመሠዊያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው።

8፤ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ።

9፤ አደባባዩንም አደረገ፤ በደቡብ ወገን ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ የተፈተለ የጥሩ በፍታ መጋረጆች ነበሩ።

10፤ ከናስ የተሠሩ ሀያውን ምሰሶችና ሀያውን እግሮች አደረገ፤ የምሰሶቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ።

11፤ በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ ከናስም የተሠራ ሀያ ምሰሶችንና ሀያ እግሮችን፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።

12፤ በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ አሥሩንም ምሰሶች፥ አሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።

13፤ በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች አደረገ።

14፤ በአንድ ወገንም የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ።

15፤ እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ አሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ሦስትም ምሰሶች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ።

16፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጆች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር።

17፤ የምሰሶቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶችም ጕልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው።

18፤ የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ነበረ፥ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጆች አምስት ክንድ ነበረ፤

19፤ ከናስ የተሠሩ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኩላቦቹ የብር ነበሩ፤ ጕልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር።

20፤ የማደሪያውም ካስማዎች በዙሪያውም ያለ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ።

21፤ በሙሴ ትእዛዝ ለሌዋውያን ማገልገል ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ እንደ ተቈጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው።

22፤ ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

23፤ ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም የቅርጽ ሠራተኛና ብልህ ሠራተኛ፥ በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ፥ በጥሩም በፍታ የሚሠራ ጠላፊ ነበረ።

24፤ የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ በመቅደሱ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።

25፤ በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ።

26፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የሰቅል ግማሽ ከተቈጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ።

27፤ መቶውም የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶውም መክሊት መቶ እግሮች አደረገ፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ነበረ።

28፤ ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶቹን ኩላቦችና ዘንጎች አደረገ፥ የምሰሶቹንም ጕልላቶች ለበጠ።

29፤ የተሰጠውም ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።

30፤ ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥

31፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የማደሪያውንም ካስማዎች ሁሉ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።